13ኛው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ክልላዊ የጥናት እና ምርምር ሲምፖዚየም በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመውን ስብራት ለመጠገን እና ዘላቂነት ያለው የትምህርት ልማት ለማስመዝገብ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ ላይ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ መምህራን ትውልድን የመቅረጽ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ ምቹ ኾነው መገኘት እንዳለባቸው የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች ለዚህ ተግባር ተፈጻሚነት ደግሞ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ትኩረት እንዳለ ኾኖ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።
የደብረ ብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራንን በማፍራት ሂደት ውስጥ ታሪካዊ ተቋም መኾኑንም አስታውሰዋል፡፡
የትምህርት ዘርፍ ላይ ያሉ ዝንፈቶችንም ለመቅረፍ ተቋሙ አቅሙን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የትኛውም ዓለም የተገነባው ትምህርትን በዋና መሳሪነት ተጠቅሞ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ትውልድ ላይ አጥብቆ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
ከመማር ማስተማር በተጨማሪ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ፋይዳቸው የጎላ በመኾኑ የትምህርት ማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ጤናማ እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመገንባት ከትምህርት ዘርፉ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ትውልድ ባሕሉን እና እሴቱን ጠብቆ በፈጠራ የታገዘ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ጥራት እና ቀጣይነት ያለው የመማር ማስተማር ምህዳር መፈጠር አለበት ነው ያሉት፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ከተማ መኾኗን ያነሱት ዶክተር አሕመዲን ውድድር ባለበት በዚህ ዘመን ተጨባጭ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ከትምህርት ተቋማት እንዲወጡ እና ለማኅበረሰቡ መፍትሄ እንዲያመጡ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
5.ቲክቶክ @amharaeducationbureau

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *