ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው 13 ኛው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ክልላዊ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም በዛሬው እለት ተጠናቋል።
የኮሌጁ ዲን መብአ ፈጠነ ( ረዳት ፕሮፌሰር) እንደገለፁት ሲምፖዚየሙ በክልሉ ከሚገኙ 10 መምህራን ትምህርት ኮሌጆች አመራሮችና መምህራን በተገኙበት ሲካሄድ የሰነበተ ሲሆን በአዘጋጁ ደብረብርሃን ትምህርት ኮሌጅ የተከናወኑ ስራዎች የህንፃ ግንባታ ምርቃት የተቀናጀ እርሻ የማዘመን ስራ የወተት ልማት ንብ የማነብ የህፃናት ማቆያ ሞዴል አፀደ ህፃናት ተጎብኝቷል፤የልምድ ልውውጥ ተካሂዶበታል።
በሲምፖዚየሙ 20 የጥናትና ምርምር ውጤቶች በተመራማሪዎች ቀርበው በቨርቸዋል ሚቲንግ ጭምር ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
ጥናቶቹ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ኮሌጆች እንዴት ውጤታማ ሆነው መገኘት አለባቸው እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎትን ማጠናከር ላይ ያጠነጠኑ መሆናቸው ተገልጿል።
ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠትና ተማሪዎችም ከመቀበል አንፃር ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማድረግ በአግባቡ ተምረው ወጥተው ሰላማዊ የሆነ ትውልድ መቅረፅ እንደሚኖርባቸውም ረዳት ፕሮፌሰር መብአ አሳስበዋል።
የደሴ መምህራን ኮሌጅ ዲን ሃሰን ወርቁ (ዶክተር) እንደተናገሩት የደብረብርሃን ትምህርት ኮሌጅ አንጋፋ መሆኑን ጠቁመው በዚያው ልክ በርካታ ሞዴል ስራዎች ተሰርተዋል፤ልምድ የወሰድንባቸውም ናቸው ብለዋል።
በትምህርት ኮሌጆች ውስጥ የመማር ማስተማር፣ጥናትና ምርምር ማድረግና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ማጠናከር የሚሰሩ ስራዎች ሲሆኑ እነዚህ ተቀናጅተው ልምድ ልውውጥ ተደርጎባቸዋል ብለዋል፤ በተለይ ሰላም ለመማር ማስተማር ስራው ወሳኝ በመሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን መውጣት አለባቸው ሲሉም አክለዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ልሳነወርቅ ተስፋሁን በበኩላቸው በሲምፖዚየሙ መልካም የሚባሉ የልምድ ልውውጥ እንደተደረገባቸው ገልፀው ይህን መልካም ተሞክሮ ወደየአካባቢያቸው በማስፋት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን የሚጠበቅባቸውን ጥራትን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ስራ መፍትሄ አፍላቂ የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እና የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ የተጠናከረ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በማጠቃለያውም የተወዳደሩ የጥናትና ምርምር አቅራቢ ተመራማሪዎች የእውቅና ሰርተፊኬትና እና ከ 6 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ሽልማት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።
በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞችና መሰረተ-ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሀመድ (ዶ.ር) የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ እንዲሁም ሌሎች የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።




