“ሁሉም የልማት ተግባራት ሰላማዊ አውድን ይፈልጋሉ” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወረታ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ የልማት ሥራዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክርቤት ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በአዲስ ዘመን ከተማ አሥተዳደር እና በወረታ ከተማ አሥተዳደር የትምህርት እና የጤና ተቋማትን መመረቃቸውን ተናግረዋል። የትምህርት ተቋማት ትውልድ እንዲቀረጽ እና ሀገር እንዲገነባ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የትምህርት እና የጤና ተቋማት ከሌሎች የልማት ሥራዎች የላቀ ፋይዳ አላቸው ነው ያሉት። የወደፊት ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ተቋማቱ በትብብር በመሠራታቸው የመንግሥት እና የሕዝብን ትስስር የሚያሳዩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። “በትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ አማካኝነት የትምህርት ተቋማት እየተገነቡ መኾናቸውን ገልጸዋል። መንግሥት ለትምህርት ተቋማት ግንባታ እና ለትውልድ ቀረጻ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል።
“ሁሉም የልማት ተግባራት ሰላማዊ አውድን ይፈልጋሉ” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ትምህርት እና ጤና ደግሞ በተለየ መልኩ ሰላምን ይፈልጋሉ ነው ያሉት። በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን አንስተዋል። ይህ ደግሞ ክልሉ ተወዳዳሪ እንዳይኾን ያደርገዋል ነው ያሉት።
ትምህርት እና ጤና ሰላማዊ አውድን ይፈልጋሉ ስንል ሰላምን በማረጋገጥ ሰላማዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አለብን ማለት ነው ብለዋል። በክልሉ የገጠመውን ችግር ለመፍታት በተሠራው ሥራ የተሻለ የሰላም አውድ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ይህን ካላደረግን በቀጣይ ተወዳዳሪነታችን ላይ መፍረድ ነው ብለዋል። ክልሉ በትምህርት እና በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንዲኾን ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የወረታ እና አካባቢው ማኅበረሰብ ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ሥራዎችን መሥራቱን ነው የተናገሩት። ከመንግሥት ጋር በመኾን ሰላምን ማረጋገጥ ሲቻል የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ይፈታሉ ብለዋል። በከተማዋ የተነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱም አንስተዋል።
ሰላም እንዲረጋገጥ ስለሠራችሁ ምስጋና ይገባችኋል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እየገቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጫካ የሚገኙ ቀሪ ታጣቂዎችን እየመከሩ የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በወረታ ከተማ አሥተዳደር የተማሩ መሪዎች ትምህርት ቤት በመገንባት ለመጪው ትውልድ አስተዋጽኦ አሳርፈዋል ነው ያሉት። ላደረጉት ነገር ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። ከችግር ጎን ለጎን የትምህርት ተቋማትን እየገነቡ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
የትምህርት ተቋማቱ በሂደት ትውልድን የሚያንጹ ናቸው ብለዋል። ትምህርት የተማረ የሰው ኃይል በመገንባት በሂደት የሕዝብን ችግር የሚፈታ መኾኑን ነው ያነሱት። የዞኑ ሕዝብ ጽንፈኝነትን እየታገለ ልማትን ማፋጠን እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በዞኑ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጽንፈኛው ቡድን አባላት ሰላምን መርጠው እየገቡ መኾናቸውን አንስተዋል። የዞኑ ሕዝብ ሰላምን እያረጋገጠ ልማቱን እንዲያስቀጥል አሳስበዋል።
የወረታ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት ፈረደ ወረታ ከተማ የሃብት ማዕከል መኾኗን ገልጸዋል። ወረታ ትርፍ አምራች እና በቱሪዝም ሃብት የተከበበች መኾኗን ነው የተናገሩት። ወረታ ከተማ አሥተዳደር ደረቅ ወደብ ያላት እና በእድገት ላይ ያለች ከተማ ናት ብለዋል።
የወረታ ከተማ አሥተዳደር ከኅብተሰቡ ጋር በመተባበር የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በከተማዋ ሆስፒታል እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባቱን ተናግረዋል።
የወረታ ከተማ አሥተዳደር የአካፋይ መንገድ እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል። የከተማ ሽግግር እንዲኖርም ጠይቀዋል።
አሚኮ