*********,*
ነሐሴ 6/2017(ትምህርት ቢሮ) የአብክመ ትምህርት ቢሮ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪ ምዝገባ ንቅናቄን ከዞን የትምህርት መምሪያ የማኔጅመንት አባላት፣ መምህራን ማህበር አመራሮች እና የተማሪ ወላጅ ተወካዮች በተገኙበት በዙም ውይይት አካሂዷል፡፡
በዙም ውይይቱ ተገኝተው የስራ መመሪያና አቅጣጫ የሰጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) እንደገለጹት በ2018ዓ.ም የትምህርት ዘመን አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን የለበትም ይህም ተግባር እንዲሳካ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ትምህርት የሁሉም አካል አጀንዳ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው መክረማቸውን ሃላፊዋ በውይይቱ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣይ በሚሰሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ያለፉ አመታት የትምህርት ብክነቶችን የሚያካክስ የትምህርት ስራ መሰራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የ2018 የተማሪ ፓይለት ምዝገባ ተግባር ከነሐሴ 15-16/2017 በተደራጀ አግባብ ይካሂዳል ያሉት ሃላፊዋ በክልሉ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ አዲስና ነባር ተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 19-30/2017ዓ.ም ድረስ በልዩ ንቅናቄ እንደሚካሄድ አጽንኦት ሰጥተው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በክልሉ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ለማስመዝገብና ትምህርት ለማስጀምር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም የክልሉ ማህበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ ዶ/ር ሙሉነሽ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *