ነሐሴ 8/12/2017 ዓ.ም /ትምህርት ቢሮ/ ኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ውጭ እንዳይሆኑ ለማስቻል 3 ሽህ 4 መቶ ሰማንያ ደርዘን ደብተር ድጋፍ አድርጓል።
ድርጅቱ በመስከረም 16 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊዎችና ተውካዮች በተገኙበት የድጋፍ ርክክብ አድርጓል፡፡
የመስከረም 16 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ሸህ አደም ሙሐመድ የተደረገው ድጋፍ የብዙ ወላጆችን እና ተማሪዎችን ችግር የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን የፋይናንስ እና አስተዳደር ስራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ሙሉጌታ ድርጅቱ አገልግሎቱን ከማዳረስ በተጨማሪ ከሚያገኘው ገቢ ላይ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለትምህርት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ኢትዮ ቴሌኮም ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ውጭ እንዳይሆኑ ለማስቻል ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ድጅታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ፣ ድጅታል ቤተ መጽሃፍትን በመገንባት እና ተከታታይ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ትምህርትን እየደገፈ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
በትምህርት ላይ የገጠመንን ፈተና በወጣት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ለመመለስ የትምህርት ቁሳቁስ አስፈላጊ በመሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች በአንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ የንቅናቄ መርሃ ግብርን በመቀላቀል ድጋፍ እንዲያደርጉ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *