ነሐሴ 18/2017ዓ.ም /ትምህርት ቢሮ/ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን አስመልክቶ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ /ፒኤችዲ / ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን 7,445,545 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መዘጋጀቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ /ፒኤችዲ / አስታውቀዋል። የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ እና ትምህርት መስከረም 5 እንደሚጀመር ኃላፊዋ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ትምህርት ሀገራችን በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሀብት በማቅረብና በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከቱ ተወዳዳሪ የሆነና በቴክኖሎጂ አቅም የበለጸገ ማህበረሰብ በማፍራት በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡
የክልላችን ትምህርት የሚጠበቅበትን የሰለጠነ የሰው ሀብት በማፍራት ረገድ ባለፉት አመታት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲፈተን ቆይቷል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቤቶች ቀደሞም ቢሆን ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ችግሮች ያለባቸውና ይህም በትምህርት ጥራቱ ላይ የራሳቸው ተጽዕኖ ያሳደሩ ቢሆንም ኮቪድ፣ ጎርፍ/ድርቅ፣ የሰሜኑ ጦርነትና አሁናዊ የክልሉ የሰላም እጦት ችግር የክልሉን ትምህርት በከፍተኛ ሁኔታ ፈትኗል ብለዋል።
በአሁናዊ የክልሉ ሰላም እጦት ችግር በ2016 ዓ.ም 2.5 ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው ከርመዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም መመዝገብ ከሚገባቸው ተማሪዎች መካከል 4.1ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው ከርመዋል፡፡ ይህ አሃዝ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የህዝብ ቁጥር በላይ ነው፡፡ ከአገራዊ ርእይ እና ክልሉ ካለው የመልማት አቅምና የአማራ ክልል ህዝብ ለትምህርት ከሚሰጠው ልዩ ዋጋ አንጻር የተፈጠረው ችግር ክልሉን የማይመጥን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ ክልሉን የተማረ የሰው ሃይል በማሳጣት ወደ ድህነት ቁልቁለት ይመልሰዋል፡፡ የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል፡፡
የአማራ ክልል የከፍተኛ ምሁራን መፍለቂያ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ የአማራ ክልል ከሀገር እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ ተቋማትን የሚመሩ በፈጠራ ስራቸው የተመሰከረላቸው ታላላቅ ሀሳብ አመንጭዎችና የቴክኖሎጅ ባለሙያወች የበቀሉበት ክልል ነው ብለዋል።
በዚህ ክልል ትምህርት እንዲቋረጥ ተድርጎ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው አይመጥንም፡፡ ትክክልም አይደለም፡፡ ይህም በመሆኑ ታዳጊ ልጆቻችን ለስደት፣ ጉልበት ብዝበዛ፣ ለሱስ፣ ለድብርት ተዳርገውብናል። ሴት ህጻናት ገና በለጋ እድሜያቸው እንዲያገቡ ተገደዋል። በጥቅሉ ልጆቻችን የወደፊት ርዕያቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ባልተገባ ሁኔታ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ትውልድን የሚቀርፁ መምህራን፣ የትምህርት ቤት አመራሮች እና የክልሉ ትምህርት መዋቅር ሙያተኛም በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ቀጥታ ተጎጂ ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ዘርፉ የሰው ሀይል የሞት ፣የአካል ጉዳት፣ እገታ እንዲሁም ሃብትና ንብረታቸውን እንዲያጡ ከመሆኑ ባሻገር ለማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡
በመሆኑም ከዚህ ችግር በአጭር ጊዜ በመውጣት በ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት እምርታ የምናስመዘግብብት ዘመን መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ለዚህም አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች እድሜያቸው ለትምህርት ደረሱ ህጻናትን በሙሉ ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፓይለት ምዝገባ የእቅዳቸውን 100 ፐርሰንት ያሳኩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም መተባበርና እንደአንድ ቃል ተናጋሪ እንደአንድ አካል መስካሪ ከሆንን የማይቻል ነገር እንደሌለ ትምህርት አግኝተናል፡፡
በክረምት ቅድመ ዝግጅት ወቅት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን፣ መምህራንና ዜጎችን በማሳተፍ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትና በርከት ያሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን መሰብሰብ ችለናል፡፡ የመማሪያ ክፍሎችን መጠገን ተችሏል፡፡
የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ችግሮችን ለማቃለል ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
በ2018 የትምህርት ዘመን በማህረሰባችን ዘንድ ትምህርት እንዲጀመርለት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን 7,445,545 ተማሪዎችን በመመዝገብ ለማስተማር እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *