የምዝገባ ሂደቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮች እና የክልሉ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት ታጀበ አቻምየለህ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በጠይማ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ ያገኘናቸው አቶ ወርቁ አስረስ ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ በማስመዝገብ እና የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጠይማ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሙሉጌታ ባለው ትምህርት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መሰራቱን ገልጸዋል። የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት ራሱን የቻለ ግቢ ከወላጆች፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦች እና ረጅ ድርጅት ጋር በመተባበር መገንባቱን ገልጸዋል። የትምህርት ግቢ ማሳመር ጥገና ሌሎች ተግባራት መጠናቀቃቸውን ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት አጠናቆ ተማሪዎችን እየመዘገበ መሆኑን እና የትምህርት ቀን መጀመርን እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ዛሬ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ መጀመሩን ገልጸዋል።
ክልሉ ከ7.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
ለውጤታማነቱ ወላጆች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ባለድርሻ አካላት ሁሉ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *