ልጆችን ከትምህርት መነጠል ነጋቸውን ማጨለም ነው።
በአማራ ክልል የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል። በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ አላንሻ መካከለኛ ደረጃ እና በሌሎች ትምህርት ቤቶችም የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ነው።
ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ ያገኘናቸው ወላጆች ትምህርት የልጆቻችን እስትንፋስ ነው፤ ከትምህርት ከነጠልናቸው ነጋቸውን ማጨለም ነው ብለዋል። ለማስመዝገብ ቆርጠን ተነስተናል ነው ያሉት። ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት እና አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እንደሚደግፉም ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ ተወካይ ረዳት ኮሚሽነር ዘለቀ አለባቸው 799 ሺህ 701 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ትምህርት በሀገራት መካከል የእድገት ልዩነት የሚያመጣ መሠረታዊ ጉዳይ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ሁሉም ተማሪዎች እንዲመዘገቡ እና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደምስ እንድሪስ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ክልል በጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ የትምህርቱ ዘርፍ ትልቅ ስብራት ገጥሞት ቆይቷል ብለዋል። በአዲሱ የትምህርት ዘመን ችግሩን ለመቅረፍ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት በነበሩት የተማሪዎች የሙከራ ምዝገባ ከተጠበቀው በላይ ውጤት መመዝገቡንም አንስተዋል።
ትምህርትን ለማስቀጠል በየደረጃው ካሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት። ወላጆች ልጆቻቸው ባለመማራቸው ቁጭት አድሮባቸዋል ያሉት ምክትል ኀላፊው በዚህ ዓመት ልጆችን በሙሉ አቅም ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ተነሳስተዋል ብለዋል።
ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን እንደ ክልል መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ትምህርት ቤቶችን የማደስ እና የመማሪያ ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ ከመሥራት ባሻገር የመምህራንን አቅም የማሳደግ ሥራ በክረምቱ ተከናውኗልም ነው ያሉት።
አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾን ሁሉም አካል ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ዘገባው የአሚኮ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *