ነሐሴ 18/2017ዓ.ም /ትምህርት ቢሮ/ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥተዋል።
በየ2018 የትምህርት ዘመን 7,445,545 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መዘጋጀቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ /ፒኤችዲ / አስታውቀዋል።
የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ እና ትምህርት መስከረም 5 እንደሚጀመር ኃላፊዋ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ይህ እቅድ እንዲሳካም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ኃላፊዋ የሚከተለውን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን አስፈላጊውን የትምህርት ቁሳቁስ አሟልተው ወደ ትምህርት ቤት ሂደው ማስመዝገብ አለባቸው፡፡ ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን መማራቸውንም መከታተል ይገባቸዋል፡፡
ወላጆች የትምህርት ቤት ችግሮችን በቅርበት ካለው የትምህርት ቤት አመራሮችና መምህራን ጋር እየተገናኙ በመፍታት የልጆቻቸው ነገ ተስፋ ማለምለም ይኖርባቸዋል።
ምክንያቱም የህጻናት ነጋቸውን የምናበራው በትምህርት ነው፡፡
ትምህርት ቤቶች የአካባው ማህበረሰብ ሀብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት በማሟላት፣ ደህንነታቸውን በመጠበቅ ረገድ ማህበረሰቡ ሚናውን መወጣት አለበት፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ የህብረተሰብ ተሳትፎን በማሳደግ የትምህርት ተቋማት ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መንገድ ስራቸውን እንዲሰሩ በማድረግ ማናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ማህበረሰቡ የትምህርት ቤቶችን ደህንነት በመጠበቅና በማስጠበቅ ረገድ ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡
መምህራንና የትምህርት አመራሩ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንደመገኘታቸው መጠን ቀጣዩ ትውልድ ተወቃሽ ላለመሆን ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትውልድ የማነጽ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከመቸውም ጊዜ በላይ ታላቅ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ሃላፊነታቸውንም ለቀጣዩ ትውልድ ሲሉ ያለምንም ማመንታት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መምህራንና የትምህርት አመራሩ ባገባደድነው ክረምት የአቅም መገንቢያ ስልጠናዎች ወስደዋል፡፡ በስልጠናዎች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ትምህርትታቸውን እንዲከታተሉ በማድግ ረገድ ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው፡፡
አጋር ድርጅቶች አማራ ክልል ትምህርት ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እየደረሰበት ላለው መደነቃቀፍና ውድመት አቅማቸው የፈቀደውን ያህል አለም አቀፍ ተቋማትን ጭምር በማስተባበር ሀብት የማሰባሰብና የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በመገንባት፣ የውስጥ ቁሳቁሳቸውን በማሟላት፣ ለመምህራንና የትምህርት አመራሮች እንዲሁም ተማሪዎች ስነልቦና ድጋፍና ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች በሙሉ የአማራ ክልል ትምህርት ወደ ቀደምት ከፍታው እንዲመለስ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ማገዝ ያስፈልጋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮና እስከ ታች ድረስ ያለው የትምህርት መዋቅርና መንግስት የባለፉ አመታት የትምህርት ብክነቶችን ሊያካክሱ የሚችሉ ስራዎችን ለመስራት የተዘጋጀ ሲሆን በተለይ የተከሰተውን የትምህርት ብክነት ለማካካስ እና የትውልድ ክፍተትን ለመቅረፍ የተፋጠነ እና አማራጭ የመማር ስልት አዘጋጅተናል፡፡
ይህንንም በመተግበር የባከኑ የህጻናትን ሁለት አመታት ለማካካስ ጥረት እናደርጋለን።
የ2018 የተማሪ ምዝገባ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ነሐሴ 19/2017ዓ.ም ይጀምራል፡፡
ትምህርት ደግሞ መስከረም 5/2018 ዓ.ም የሚጀምር በመሆኑ ሁሉም ማህበረሰብ በትምህርት ቤት በመገኘት ቅዱሱ የትምህርት ስራ እንዲሳካ ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
ትምህርት ለትውልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *