ይህ ወቅት ልጆች ለወራት ከትምህርት ቤት የራቁበት ነው። ወደ ናፈቁት ትምህርት ቤት ለመመለስ የሚጓጉበት ጊዜም ጭምር።
እኔም ወደ አንዱ የገጠር መንደር አቅንቻለሁ። ዙሪያ ገባውን እየቃኘሁ ወደ አርሶ አደር ልብስነው ንጉሴ ማሳ ዘለቅሁ። አርሶ አደሩ የአካባቢው መገለጫ በኾነው ፍቅር በተሞላበት አቀባበል ተቀብለው አስተናገዱኝ።
ፍቅር በተሞላበት አቀባበላቸው እየተደነቅሁ ላነሳው የወደድኩትን ጉዳይ አነሳሁ። አርሶ አደሩን ወደ ልጅነት እድሜያቸው መልሸ በማስታወስ የትምህርት እድል አግኝተው እንደኾነ ጠየኳቸው።
“አዎ ልጀ የመጨረስ እድል ባይኖረኝም እስከ 8ኛ ክፍል ደርሸ ነበር” አሉኝ። “እየውልህ ያኔ ትንሽ የትምህርት ጥቅም የገባው ሰው ቢኖርም አብዛኛው ሰው ግን ትምህርት በሄድክበት ሁሉ ቁልፍ ጉዳይ መኾኑ አልተረዳውም ነበር” አሉኝ እና ገለጻቸውን ቀጠሉ።
የቀየው ሰው እንግዲህ ትምህርት ይበቃዋል፤ አጋብተህ ጥሩ ገበሬ ይሁን እያሉ ሲወተውቱ ወላጆቸም ትምህርቱን አቋርጨ አግብቼ በእርሻ እየረዳኋቸው እንድኖር አደረጉ ሲሉ ትምህርት ያቆሙበትን ምክንያት ነገሩኝ።
ስለልጆቻቸውም ጠየቅኃቸው። ሦሥት ልጆች አሏቸው። እነዚህን ለማስተማርም ከየትኛውም የቀየው ሰው ቀድመው የሚገኙ ዕውቀት ወዳድ ሰው ስለመኾናቸው አብራሩልኝ።
ትንሽም ቢኾን በመማራቸው ዘመናዊ የእርሻ ሥራን ለመገንዘብ ቅርብ ናቸው። አዳዲስ አሠራሮችን ለመቀበል እና ለመተግበር ፈጣን ነኝ፤ ይህም ትንሽም ቢኾን በመማራቸው የመጣ ስለመኾኑ ይናገራሉ።
“ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎችንም ግብዓቶች በዕውቀት ለመጠቀም የምጥረው ስለተማርኩ ነው፤ ትምህርት ከሌለህ ብዙ ነገር ታጣለህ፤ ይህ አሁን ለኔ ግልጽ የኾነ ጉዳይ ነው” ይላሉ አርሶ አደሩ።
በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ለመኾን ትምህርት ቁልፉ ጉዳይ እንደኾነ የሚናገሩት አርሶ አደሩ ይህንንም ታሳቢ አድርገው ልጆቻቸውን እያስተማሩ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
አርሶ አደር ልብስነው ባለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት በመቋረጡ ልንቆጭ ይገባል አሉ። ባለፉት ጊዜ የተሠራው ስህተት ባለማወቅ የኾነ እና ትውልድን የሚጎዳ ነበር ያሉት አርሶ አደሩ አሁን ላይ ሁሉም ቆም ብሎ ልጆቹን የሚጎዳ ተግባር ከመፈጸም መቆጠብ እንዳለበት መክረዋል። ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንደሚገባም ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ የነበረው ውዥንብር አሁን እየጠራ፣ ትምህርት መቋረጡ ትክክል እንዳልኾነም ሁሉም እየተረዳ ነው፤ ወደ ትምህርት ቤት ልጆቹን ለመላክ እየተዘጋጀን ነው ሲሉም አስረድተዋል።
እሳቸው ከዚህ በፊት ልጃቸውን ትምህርት በሚገኝበት ከተማ ልከው ቀለሙን እንዳይረሱ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው በዚህ ዓመት ግን ከቀየው ሰው ጋር መክረው ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት መስማማታቸውን እና ይህን የሚያውኩ ኀይሎችንም እየመከሩ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
የእርሳቸው እጣ በልጆቻቸው እንዳይደገም ዛሬ ላይ ሁሉንም መስዋዕትነት በመክፈል ለማስተማር ዝግጁ  መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
ተማሪዎች በምዝገባ ላይ
      ተማሪዎች በምዝገባ ላይ
አቶ ድረስ ጫኔ የተባሉ ሌላው አርሶ አደር እርሳቸው ከሁለተኛ ክፍል ማቋረጣቸውን ገልጸው ትምህርት አለመማር ያለውን ጉዳት በሕይዎቴ አይቸዋለው ይላሉ።
ዛሬ ላይ ልጆቻቸውን በማስተማር ለቁምነገር ማብቃት ቅድሚያ የሚሰጡት የሕይዎት መስመር መኾኑንም ነግረውናል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት በመቋረጡ የልጆቻቸውን እድሜ እና ሕይዎት መቀነሱን ገልጸው ይህ ጉዳት የበለጠ እንዳይኾን ከአሁኑ በቀየው መክረው ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱና ተማሪዎች እንዲመዘገቡ እያደረጉ ስለመኾኑ ነግረውናል።
“የትምህርት ጥቅም የገባኝ ከግብርና የሚመጡ ዘመናዊ አሠራሮችን አንብቤ ባለመረዳቴ ነው” የሚሉት አርሶ አደሩ ወደ የትኛውም የሥራ ዘርፍ ለመሄድ ትምህርት መሠረታዊ ነገር ነው ይላሉ።
ዛሬ ላይ አራት ልጆቻቸውን በማስተማር የነጋቸውን ሕይዎት ለማሳመር የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ መሰረት የ2018 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ተጀምሯል። እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ይቀጥላል።
በትምህርት ዘመኑ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱንም ነው ቢሮው የገለጸው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ለትምህርት ዘመኑ የተማሪዎች ምዝገባ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
ቢሮ ኀላፊዋ በትምህርት ጉዳይ ላይ አሁን የተፈጠረው የማኅበረሰቡ ቁጭት፣ የአጋር አካላት ድጋፍ እና በየደረጃው ያለው ቅድመ ዝግጅት የታቀደውን ውጤት ለማሳካት አቅም ይኾናል ብለዋል።
የዚህ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራም መስከረም 05/2018 ዓ.ም እንደሚጀምር ቢሮ ኀላፊዋ ለአሚኮ ገልጸዋል።
ዘገባው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *