በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት እና እውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
መስከረም 19/2018 ዓ.ም /ትምህርት ቢሮ/ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማትና እውቅና የመስጠት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩም በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 452 ተማሪዎች እና ከ400 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 3 አይነ ስውር ተማሪዎች ተሸልመዋል።
በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ /ዶክተር/ የትኛውም ስኬት በአንድ ጀንበር የሚመጣ ሳይሆን በየቀኑ ትናንሽ እርምጃዎችን የመውሰድ ወደ ኋላ የማይል ጽናት የማሳየት እና ከስህት የመማር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተሻላሚዎች እነዚህን ሂደቶች አልፋችሁ መጥታችኋል። የዛሬው ስኬታችሁ የጉዞአችሁ መጀመሪያ በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ለመትጋት፣ አሸንፎ ለመውጣት ፣ ከተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ራሳችሁን በማላመድ፣ በስነልቦና ዝግጁ በመሆን ለሌሎች አርዓያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል ።
በ2017 የትምህርት ዘመን በትምህርት ተሳትፎና ፍትሐዊነት ረገድ የገጠመውን ፈተና ለማለፍ በርካታ ስራዎችን ለመስራት ጥረት ተደርጓል። በተለይ ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የትምህርት መዋቅሩ የተቻለውን ድጋፍ እና እገዛ ማድረጉን አውስተዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን ፈተና ከወሰዱ 94,668 ተማሪዎች መካከል 12.5% ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት አስመዝግበዋል። 452 ተማሪዎች 500 እና በላይ ውጤት አስመዝግበዋል። ይህም እንደ ሀገር ከተመዘገበው 8.4% አማካይ ውጤት በላይ ነው። ካለፈው አመት ውጤት አንጻርም ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። ከአሳለፍነው ፈተና አንጻር እጅግ የሚያኮራ ውጤት ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን /ዶክተር/ ዛሬ የታላቅ፣ የኩራት እና የመነሳሳት ቀን ነው ተሻላሚዎች በላቀ ትጋት ትኩረት ሰርተው ውጤት በማስመዝገባቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ታላላቅ ስኬቶች በታላላቅ ፈተናዎች ውስጥ እንደሚወለዱ የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ትምህርት የሀገር ግንባታ መሰረት እና የፈጠራ በሮች የሚከፈቱበት ቁልፍ ነው ፣ ችግርና ቀውስ ባለበት ዘመን ደግሞ እዉቀት ከችግር የሚያወጣ ዘላቂ መንገድ መሆኑን በጽኑ ይገነዘባል በመሆኑም ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *