በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ /ዶክተር/ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተሸላሚ ተማሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት።
ውድ ተሸላሚ ተማሪዎች የትኛውም ስኬት በአንድ ጀንበር የሚመጣ አይደለም።በየቀኑ ትናንሽ እርምጃዎችን የመውሰድ ወደ ኋላ የማይል ጽናት የማሳየት እና ከስህት የመማር ውጤት ነው። ተሻላሚዎች እነዚህን ሂደቶች አልፋችሁ መጥታችኋል። የዛሬው ስኬታችሁ የጉዞአችሁ መጀመሪያ በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ለመትጋት፣ አሸንፎ ለመውጣት ፣ ከተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎች ራሳችሁን በማላመድ፣ በስነልቦና ዝግጁ በመሆን ለሌሎች አርዓያ መሆን ይጠበቅባችኋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን በትምህርት ተሳትፎና ፍትሐዊነት ረገድ የገጠመንን ፈተና ለማለፍ በርካታ ስራዎችን ጥረት ተደርጓል። በተለይ ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የትምህርት መዋቅሩ የተቻለውን ድጋፍ እና እገዛ ተደርጓል። በዚህም በ2017 የትምህርት ዘመን ፈተና ከወሰዱ 94,668 ተማሪዎች መካከል 12.5% ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት አስመዝግበዋል። 452 ተማሪዎች 500 እና በላይ ውጤት አስመዝግበዋል። ይህም እንደ ሀገር ከተመዘገበው 8.4% አማካይ ውጤት በላይ ነው። ካለፈው አመት ውጤት አንጻርም ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። ይህም ካአሳለፍነው ፈተና አንጻር እጅግ የሚያኮራ ውጤት ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ።
በ2017 የትምህርት ዘመን ሰባት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ አሳልፈዋል።
ይህ ውጤት እንዲመዘገብ ከላይ እስከ ታች የሰራችሁ የትምህርት መዋቅራችን፣ ሌት ተቀን የሰራችሁ እንቁ ተማሪዎቻችን፣ መምህራንን፣ ድጋፍ ያደረጋችሁ የክልል አስተባባሪዎች፣ ወላጆች በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።
ስለትምህርት ስናነሳ ሁልጊዜም ማይረሳው ጉዳይ ስለ ቀጣዩ ትውልድ እና ሀገር ሰላም፣ ልማት፣ ብልጽግና ማሳኪያ መንገድ ቁልፉን እየፈለግን መሆኑን ነው። የትምህርትን ጥራት፣ ተገቢነት እና ተደራሽነት ሳያረጋገጥ ያደገ፣ የለማ፣ የበለጸገ ሀገር የለም።
ውድ ተሸላሚዎች የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተማሪዎች በመሆናችሁ ከእናንተ የሚጠበቁ ቁልፍ ባህሪያት ውስጥ ጥቅቶቹን ላስታውሳችሁ።
1. ትብብር :- ትብብር የዘመናዊ ዓለም ተፈጥሮዊ ትስስር የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ ክህሎት በአካልም ሆነ በተጨባጭ በቡድን ውስጥ በብቃት የመስራት ችሎታን ያካትታል። የትብብር ተማሪዎች የጋራ ግቦችን ለማሳካት በመግባባት ፣ሃሳቦችን በመጋራት እና ሀብቶችን በማዋሀድ የተካኑ ናቸው።
2. ፈጠራ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ትምህርት ላይ ቁልፍ እና ወሳኝ ነው። በተማሪዎች ውስጥ ፈጠራን ማበረታታት የማወቅ ጉጉትንና የህይወት ዘመን የመማር ፍቅርን ያሳድጋል።
3. ሳይንሳዊ አስተሳሰብ መረጃን በጥንቃቄ እና በማስተዋል መተንተን መገምገም እና ማዋሀድ መቻል ነው።
4. አለም አቀፋዊ ዜግነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተማሪዎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ባህሎችንና አመለካከቶችን በማወቅና በመረዳት ይታወቃሉ። ለዚህ ደግሞ የማስተማር፣ የመጻፍ ችሎታ እና ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ አስፈላጊ ነው።
ክብራን እና ክቡራት
እረጅም ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል እንዲሉ የልጆቻችንን የወደፊት የትምህርት ህይወት የሚጀምረው ዛሬ ላይ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ትምህርት ቤት ስናስመዘግባቸው ነው። በስነ ምግባር የተመሰገኑ፣ በአመለካከት እና በእውቀት የዳበሩ ቴክኖሎጅን የሚጠቀሙ ፣ ስራ ፈጣሪ እና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ለማፍራት እኔ እና እናንተ ሀላፊነት አለብን።
በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *