“ትምህርት የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት፣ ክብር እና ማንነት ማስጠበቂያ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ መሪዎች በደቡብ ጎንደር ዞን አዲስ ዘመን ከተማ አሥተዳደር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነባውን የማስፋፊያ ሕንጻ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ትውልድን ለመገንባት ጊዜያዊ ችግር አይበግረንም ብላችሁ ትምህርት ቤት በመገንባታችሁ ክብር ይገባችኋል ነው ያሉት።
ትምህርት የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት፣ ክብር እና ማንነት ማስጠበቂያ ነው ብለዋል። ያልተማረ ሀገር እና ሕዝብ የትም እንደማይደርስ ገልጸዋል። ለትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ትኩረት የሰጡ ሀገራት ማደጋቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መኾኑንም ገልጸዋል። ከጥንት ጀምሮ ድንጋይ ጠርቦ፣ ቀለም በጥብጦ ዕውቀትን ሲዘራ መኖሩን ነው የተናገሩት።
አኹን ላይ ግን ያለ ልምዱ እና ክብሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ፈርሰውበታል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል ነው ያሉት።
ይህን ያደረጉት የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ናቸው ብለዋል። ይህ አካሄድ ለሕዝብ አይጠቅምም ያሉት ኀላፊዋ ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል። በቃህ በማለት ልጆቻችን ማስተማር አለብን ነው ያሉት።
ያልተማረ ሕዝብ የትም እንደማይደርስ ገልጸዋል። የመማር ማስተማር ሥራዎችን የሚከለክሉ አካላትን መምከር እና በቃ ማለት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን እየገሰጹ እንዲመልሱም አስገንዝበዋል።
መተባበር እና አንድነት ካለ የትኛውንም ችግር መወጣት እንችላለን ነው ያሉት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥለሁን ደጀኔ ሰላማችን እያረጋገጥን የልማት ሥራዎች እየሠራን ነው ብለዋል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሕዝብን በቅንጅት ማገልገል አሸናፊ ያደርጋል ነው ያሉት።
የአዲስ ዘመን ከተማ አሥተዳደር እና የሊቦ ከምከም ወረዳ በፍቅር፣ በአንድነት እና በመተሳሰብ ያማረ ትምህርት ቤት ገንብተው ማስመረቃቸውንም ገልጸዋል።
አንድነት እና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
የሊቦ ከምከም ወረዳ አሥተዳዳሪ ታዘብ አበበ በወረዳው ልማትን ለማፋጠን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አካባቢው ለልማት የተመቸ መኾኑን ተናግረዋል።
ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም ተናግረዋል። በወረዳው በትጥቅ ትግል ያሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሰላም ለመጠበቅ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ከሕዝብ ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ የጽንፈኛውን ቡድን በደል በመቃወም ለሰላም እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመከላከል፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመማር ማስተማር ሥራው መልካም ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ ዘመን ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ተገንብቶ መጠናቀቁንም አመላክተዋል።
ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። ትምህርት ቤቱ በርካታ ተማሪዎችን የሚቀበል በመኾኑ አኹንም ተጨማሪ ግንባታ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *