የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከህዳር 13-14/2013ዓ.ም ለምዕራብ ጎንደር፣ ጎንደር ከተማ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ባህርዳር ከተማ አስተዳደር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች በቀውስ ወቅት ትምህርትን መምራት በሚል ርዕስ በደብረታቦር ከተማ የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት የአብክመ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሲሆኑ ቀውስና የቀውስ ባህሪዎች ምልከታ ምን እንደሆኑና ቀውስ ማለት የተለመደውን መደበኛ አሰራርን ወይም ህይወትን የሚያውክ ወይም እንዳይቀጥል የሚያደርግ ሰው ሰራሽ ወይም ተፈጥሯዊ ክስተት መሆኑን ተብራርቷል፡፡
የትምህርት አመራሩ የቀውስን ምንነት ተረድቶ ትምህርት ቤቶችን በተገቢው መንገድ መምራት ያለባቸው መሆኑን ተገልዿል፡፡ ሁሉም ቀዉሶች በህጻናትና በትምህርት ቤቶች ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ወይም ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ ይህንን በማወቅ ተገቢውን ቀውስ ምላሽ ተግባራትን መስራት ተገቢ እንደሆነ በስልጠናው ቀርቧል፡፡ በተያያዘም የትምህርት አመራሩ የቀውስ ባህሪዎችን አውቆ መደበኛ ስራውን መስራት ያለበት መሆኑንና የቀውስ ወቅት አመራርን ለማሳካት መሰረታዊ የሆኑ መርሆዎችን ማወቅና መተግበር ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራር ባህሪ መሆን እንዳለበት በስልጠናው ቀርቧል፡፡
በመቀጠልም የ2013ዓ.ም መማር ማስተማሩን የተመለከቱ ተግባራት ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊዎችም የስልጠናውን ወቅታዊነትና አስፈላጊነት በተመለከተ የክልሉን ትምህርት ቢሮ አመስግነው ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በአብክመ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የተሰጠ ሲሆን በማብራሪያቸውም አሁን ያለነው በቀውስ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ወቅቱን የሚመጥን ስራ መስራት እንደሚገባና ኮቪድን በትምህርት ቤቶች በመከላከል ረገድም የኮቪድ ፕሮቶኮሎችና መከላከያ ዘዴዎችን መተግብር፣ አሁን ከገጠመን ችግር አኳያም ከእኛ የሚጠበቀው መደበኛ ስራችንን ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ በመስራት መደገፍ በሚገባን ጉዳይ እየደገፍን መሄድ እንደሚገባ ገልጸው የትምህርት አመራሩ በጥናት፣ በቁርጠኝነት፣ በአቋም፣ በራስ መተማመን ስሜት ሆነን ስራችንን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶችን የገጽታ ችግር ያነሱት ሃላፊው በ2012ዓ.ም ከአልማ ጋር በመሆን የተሰራው ስራ አበረታች እንደነበር አስረድተዋል፡፡ የትምህርት ቤቶችን የገጽታ ችግር በቀጣዮቹ አመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በአልማ የተጀመረውን ስራ በመደገፍ ገጽታቸውን መቀየር እንደሚገባ አሳስበው በቀጣይ የትምህርት አመራሮች ትኩረት አድረገው መስራት ያለባቸውን 6 ዋና ዋና ጉዳዮችን በማቅረብ ውይይቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ይህ ስልጠና በሌሎች ቀጠናዎችም የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን https://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን!!
2 thoughts on “የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡”
  1. በአማራ ክልል ለሚኙ ለሚገኙ ሁሉም ር/መመህራንና ሱፐርቫይዘር ነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተሰጠው ዘገባው ሙሉ ይሁን በአንድ አካባቢ አይወሰን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *