በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው ግዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዲጂታል መማሪያ ማእከል ተጠቃሚ ኾነ፡፡
________________________________________________
 ኢትዮ ቴሌኮም ለግዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለዲጂታል መማሪያ ማእከል የሚያገለግሉ ኮምፒውተሮች፣ የመቀመጫ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎችና 11 ሜጋባይት የኢንተርኔት አገልግሎት ድጋፍ አድርጓል። ኢትዮ ቴሌኮም በአጠቃላይ ለትምህርት ቤቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ነው ድጋፍ ያደረገው።
በግዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ እታገኘሁ አበባው ዲጂታል መማሪያ ማእከሉ ትምህርቷን በብቃት ለመማር እንደሚያግዛት ተናግራለች።
የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳሙኤል ገረመው ከአሁን በፊት ትምህርት ቤታቸው የዲጂታል መማሪያ ማእከል ተጠቃሚ እንዳልነበረ ተናግሯል። ዛሬ ግን በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ትምህርት ቤታቸው የዲጂታል መማሪያ ማእከል ተጠቃሚ መኾኑ እንዳስደሰታቸው ነው የተናገረው።
የዲጂታል መማሪያ ማእከሉ ዕውቀታቸውን እንደሚያጎለብትላቸው ተናግሯል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሙላው አበበ በክልሉ 12 ትምህርት ቤቶች የዲጂታል መማሪያ ማእከል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል ብለዋል። ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በክልሉ የተዘረጉት የዲጂታል መማሪያ ማእከላት ተማሪዎች ብቁ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ግብዓቶችን ለማሟላት ሲሠራ እንደነበረም አንስተዋል። ለትምህርት ቤቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለሚያደርገው የትምህርት ቤቶች ድጋፍ ስኬታማነት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ዳይሬክተር አበበ ጥሩነህ በኢትዮ ቴሌኮም የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለኅብረተሰቡ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል። ከማኅበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የዲጂታል መማሪያ ማእከል መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በመላ ሀገሪቱ 66 የዲጂታል መማሪያ ማእከል እንደዘረጋ ከዚህም ውስጥ 12ቱ በአማራ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር አቀፍ ደረጃ 66 ዲጂታል መማሪያ ማእከላትን በማቋቋም ተማሪዎችን ለማገዝ እና የትምህርት ጥራትን ለማሳለጥ መሥራት መጀመሩን ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል በ12 በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የዲጂታል መማሪያ ማእከላት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
በመላ ሀገሪቱ ኢትዮ ቴሌኮም ለ66 ትምህርት ቤቶች በጥቅሉ 45 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የዲጂታል መማሪያ ማእከላት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል መማሪያ ማእከላት ተጠቃሚ ለኾኑ ትምህርት ቤቶች የቴክኒክ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አቶ አበበ ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) የዲጂታል መማሪያ ማእከሉ፥ ተማሪዎች ዓለም ከደረሰበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲደርሱ ያስችላቸዋል ብለዋል። የዲጂታል መማሪያ ማእከሉ ተማሪዎች ብቁ ተወዳዳሪዎች እንዲኾኑ ይረዳቸዋል ነው ያሉት።
በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሰል እድል እንዲያገኙ ኢትዮ ቴሌኮም ድጋፉን ሊቀጥል እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የግዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ታገሰ ሌንጫሞ የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኢትዮ ቴሌኮም በትምህርት ቤታቸው ያስጀመረው የዲጂታል መማሪያ ማእከል የትምህርት አሰጣጡን እንደሚያዘምነው ተናግረዋል።
ዘገባው የአሚኮ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *