በባህርዳር ከተማ በተዘጋጀው ዓመታዊ የትምህርት ቀን ጉልህ ድርሻ ላበረከቱ መምህራንና አጋር አካላት እውቅና ተሰጣቸው።
***
“መምህራን ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክቱት ወደር የሌለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህ ተጋድሎ ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው። ” ዶ/ር ድረስ ሳህሉ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ
**
በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስተባባሪነት “ትምህርት ለሰላም ፣ሰላም ለትምህርት” በሚል መልእክት ዓመታዊ የመምህራን ቀን በመከበር ላይ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ለትምህርት ግንባታ ጉልህ ድርሻ ላላቸው መምህራን እንዲሁም ለአጋርና ባለድርሻ አካላት የእውቅና እና ምስጋና ስነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በዝግጅቱ ላይ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተብ ታፈረ፣ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ፣ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለ ማርያም እሸቴ መምህራን የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማሳለጥ ባሻገር እንደ ሀገር የገጠመንን ቀውስ ለመቀልበስ ሲደረግ በቆየው የህልውና ዘመቻ ላይ
ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ በንቃትና በትጋት በመሳተፍ ላሳዩት ጀግንነት ምስጋና አቅርበዋል።
በወራሪው ኃይል ምክንያት ከተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች ተፈናቅለው በከተማችን ለተጠለሉ ተማሪዎች ከመደበኛ እስከ ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ጥሩ ውጤት ይዘው እንዲሄዱ በማድረግ በኩልም ላበረከቱት ጉልህ ሚና በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ በበጀት ዓመቱ የትምህርት ጥራትን ከነተደራሽነት በማምጣት እንዲሁም የትምህርት ቤቶችን ገፅታ በመገንባት በኩል የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ለታዳሚው አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተብ በበኩላቸው መምህራን ለሀገር ግንባታ መሰረቶች በመሆናቸው ለዚህ ጥረታቸው እውቅናና ምስጋና መቸር ሲያንስ እንጅ አይበዛባቸውም ብለዋል።
ሀገራት ባላቸው እውቀት፣ ሀብት እና የለማ የሰው ኃይል ልክ የሚላኩ ቢሆንም ዋነኛው ግን የለማ የሰው ሀብት በመሆኑና ይህ ሰው ሀብት ልማት የሚመጣው ደግሞ በትምህርት በመሆኑ መምህራን ቀጥተኛው ተፅእኖ ፈጣሪ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ መሆኑን ገልፀዋል።
በየዓመቱ የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ማዘጋጀት ቀጣይ በሚደረገው የመማር ማስተማር ሂደቱ ስኬታማነት እና ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የትምህርት ስርዓት ለማምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ቢሮ ኃላፊው አክለውም የባህርዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ለመምህራን ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት በየዓመቱ እያደረገ ላለው እውቅናና ምስጋና የመስጠት ተግባር የላቀ ምስጋና የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት መምህርራን ግንባር ቀደም ተጠቃሽና መሪ ተዋናይ ቢሆኑም መላው ማህበረሰብ በየደረጃው የየድርሻቸውን ካልተወጣ ህዝብ የሚፈልገውና ዘላቂ የትምህርት ስርዓት ሊማጣ ስለማይችል በጋራ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑንም ገልፀዋል።
የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ መምህራን ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክቱት ወደር የሌለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህ ተጋድሎ ዋጋ መስጠት ተገቢ መሆኑን በማመን በከተማችን የሚገኙ መምህራንም ሆኑ ሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት የትምህርት ቤቶችን ገፅታ ከማበልፀግ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱም መሳለጥ ላደረጉት ርብርብ የሚገባቸውን ምስጋና እንሰጣቸዋለን ብለዋል።
መምህራን በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የስነ-ምግባር ጉድለት በማረም በኩል ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እንዲዳብር ሁሉም አካል በቅንጅት መስራትን የሚጠይቅ ጥረት መሆኑን ገልፀዋል።
በመጨረሻም ከሁሉም ትምህርት ቤት የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለወጡ ተማሪዎች የመፃህፍ እና የምስክር ወረቀት፣ ከመምህርነት ባሻገር በዘመቻ ተቀላቅለው በጋሸና፣ ማይጠብሪና መሰል ግንባሮች የተዋደቁ እንዲሁም ለሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘገባው የባህር ዳር ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *