“በአራት ቢሊዮን ብር አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ ነው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ
===============================
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአራት ቢሊዮን ብር አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሊገነባ መኾናቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በምዕራብ አማራ ዞኖች ከሚገኙ የትምህርት መሪዎች ጋር በወቅታዊ የትምህርት ሥራዎች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ ክልሉ በዚህ ዓመት አራት ቢሊዮን ብር በመመደብ በደብረ ታቦር፣ በፍኖተ ሰላም እና በሰቆጣ ከተሞች አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ 12ኛ ክፍልን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች መካከል ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ነው ያሉት ኀላፊዋ ይህን በጎ ተሞክሮ ለማስፋፋት በቢሮው በኩል እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በአዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ሰፊ ጊዜ እንዲሰጡ እና እርስ በእርስ እንዲተጋገዙ ስለሚረዳ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ በኩልም የትምህርት ጥራትን ማምጣት ስለሚቻል መንግሥት ይህን ዘርፍ አጠናክሮ እየሠራበት ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ወይዘሮ ኢየሩስ አክለውም ትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ወጭ ደግሞ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚገነባበት ቦታ እንዲሰጠው መጠየቁን ጠቁመዋል። በመኾኑም የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር የቦታ መረጣ እና ዝግጅት ሥራውን ወደ ማጠናቀቁ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል።
“ትምህርት ለትውልድ”
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *