የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2016 ዓ.ም የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ነው።
በግምገማ መድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ እንደገለፁት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከ3ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራው ተስተጓጉሎ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም አሁን ያለውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም በስራ ላይ ያልነበሩ ትምህርት ቤቶችን እንዲጀምሩ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ትምህርት እየተሰጠ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚህም ከ12 ሚሊዮን በላይ መፃህፍት ታትመው ለተማሪዎች እንዲደርሱ ተደርገዋል። ከባለፈው አመት ጀምሮ የሚገነቡ አዲስ ትምህርት ቤቶች ሁሉም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና ነባሮቹም ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመክፈቻ ፕሮግራሙ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው ትምህርት የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን በማረጋገጥ ስነምግባር የተላበሱ ምሁራንን ለማፍራት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።
በመድረኩ የጎንደር ክላስተር ዞኖች የተሳተፉ ሲሆን የትምህርት ማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *