የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም
መግቢያ
የአፍሪካ ሕብረት በቅርቡ 37ኛውን የሕብረቱን የመሪዎች ጉባዔ አካሂዷል:: በዚህ ወቅት እንደገተለጸው በአህጉሪቱ 100 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው::
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት የሚገባቸው ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ከትምህርት ውጭ ሆነዋል::
በሌላ መረጃ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (unocha.org) ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አስታውቋል:: ሪፖርቱ በተጨማሪነትም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ዘጠኝ ሺህ 160 ትምህርት ቤቶች ለጉዳት ተዳርገዋል:: ከዚህ ውስጥ 30 በመቶው በከፍተኛ ደረጃ የወደሙ ናቸው:: ይህም ተማሪዎች በዛፍ እና በፈራረሱ ሕንጻች ሥር ለመማር እንዳስገደደ አስታውቋል::
የባከኑ ዓመታት
በ2013/14 የትምህርት ዘመን በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገበውና ለጊዜው ስሙን ከመናገር የተቆጠበው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ግጭቱ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳያስቀጥል አድርጎታል:: በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ በ2015 ዓ.ም በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሲከታተል ቢቆይም የሁለተኛ ዓመት ትምህርቱን ለማስቀጠል ግን መንታ መንገድ ላይ መቆሙን ተናግሯል::
በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ምንም እንኳ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋትን የደቀነ ቢሆንም የጀመረውን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል:: ቤተሰቦቹ ግን ወደተመደበበት ዩኒቨርሲቲ እንዲሄድ አልፈለጉም፤ ይልቁንም በዩኒቨርሲቲ ለማሳካት የፈለገውን ትምህርት ከቤተሰቦቹ ሳይርቅ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንዲያሳካው ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ተናግሯል:: አሁንም መንግሥት ግጭቱን በሰላም ቋጭቶ ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ የሚመለስ ከሆነና በዩኒቨርሲቲዎች ዳግም ጥሪ ከተደረገ የልጅነት ህልሙን ለማሳካት እንደሚመለስ አስታውቋል::
የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ግጭቱ የትምህርት ዘርፉ ክፉኛ እንዲፈተን እያደረገ መሆኑን ታዝቧል:: በተለይ ግጭቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሳይቀሩ ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት እንዲቀንስ ማድረጉን ተናግሯል:: በትምህርት ላይ ያሉትም ቢሆኑ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻል ከቅርብ ጓደኞቹ በተመለከተው የፈተና ውጤት አረጋግጦለታል::
ሚሊዮኖችን ከትምህርት ውጪ ያደረገው ምንድን ነው?
ግጭት (ጦርነት)፣ መፈናቀል፣ የኮቪድ ወረርሽኝ እንዲሁም ሌሎች ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች አፍሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ተግባራዊ አደርገዋለሁ ብለው ትኩረት ለሰጡት የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ፈተናዎች ሆነው ተመላክተዋል:: ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን በመተግበር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በመትጋት ላይ ብትገኝም እስካሁን የታየ ለውጥ አለመኖሩን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራር መምህርና ባለሙያ ሸጋው ሞላ ተናግረዋል:: በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ እየታየ ላለው ችግር በርካታ ገዥ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል:: ከሁሉም በላይ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ሀገር እያጋጠመ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቁመዋል::
ባለሙያዉ እንደሚሉት ግጭት ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ለጦርነት ዓላማ እንዲውሉ ያደርጋል:: ለተጽኖው ማሳያ ያደረጉትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሽፋን እጅጉን እየቀነሰ መምጣቱን ነው:: ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ካስፈተነቻቸው ተማሪዎች ውስጥ 96 ነጥብ 7 በመቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ አልገቡም። 1ሺህ 600 ትምህርት ቤቶችም ያስፈተኗቸውን ሁሉንም አላሳለፉም::
ግጭቱ አሁንም በአማራ ክልል መቀጠሉ ክልሉ ከትምህርት ውጭ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር በጥራትና ተደራሽነት ላይ የጎላ ተጽእኖ እንደሚያሳድር መምህር ሸጋው ያምናሉ:: ለችግሩ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ካልተቻለና አሁንም ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ የክልሉ የትምህርት ሽፋን በከፋ ችግር ውስጥ ይወድቃል የሚል ስጋት እንዳላቸው አስገንዝበዋል::
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ግጭት እና ጦርነት ባሉባቸው ሀገራት ከአጋር አካላት ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለቁሳቁስ… በሚያደርጉት ድጎማ /ፈንድ/ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራል:: በዚህም ለትምህርት ተብሎ የሚመደበው በጀት /ፈንድ/ አናሳ መሆን ችግር ፈቺ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ሂደት ይገዳደረዋል:: የትምህርት ቤትም ሆነ የመማሪያ ክፍል ማስፋፊያን በመገደብ “ትምህርት ለሁሉም” የሚለው ዓላማ እንዳይፈጸምም ያደርጋል::
የምጣኔ ሀብት ችግር በተለይ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ካለው የትምህርት ቁሳቁስ፣ ክፍያ… ወጪ ጋር በተገናኘ ለኢትዮጵያ ትምህርት ዋና ፈተና መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል:: በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የቀጠሉ ግጭቶች አርሶ አደሩ ከበጋ እስከ ክረምት እንዳያመርት እክል በመፍጠር የኢኮኖሚ መሽመድመድ እንዲያጋጥም አድርገውታል:: ግጭቱ የግብርና ግብአት በወቅቱ እንዳይደርስ ከማድረግም ባለፈ የተመረተው በወቅቱ ሳይሰበሰብ የባሩድ ቀለብ መሆኑ ብዙኃኑ ለኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል:: ይህን ተከትሎ የሚፈጠረው የኢኮኖሚ ችግር ለትምህርት ዘርፉ ፈተና በመሆን ወላጅ ሁሉንም አሟልቶ ልጆቹን ለማስተማር ችግር ላይ ወድቋል፤ ችግሩን ተቋቁሞ ትምህርት የሚጀመር ቢኖርም እንኳ እስከ መጨረሻው ሳይዘልቅ ሊያቋርጥ እንደሚችል ባለሙያው ጠቁመዋል::
የትምህርት መሰረተ ልማት ችግር በተለይ የመማሪያ ክፍል እጥረት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አለመኖር፣ የመጓጓዣ ችግር እና ሌሎችም ተማሪዎች በመደበኛነት ወደ ትምህርት ተቋማት እንዳይሄዱ የሚከለክሉ ናቸው:: በቤት ውስጥ የሴቶች ከፍተኛ ኃላፊነት መኖርና ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የትምህርት ቤቶች በአቅራቢያ አለመገኘት ተጨማሪ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ችግር ሆነው እንደሚነሱ ባለሙያው ጠቁመዋል::
የሰሜኑ ጦርነት፣ በተፈጥሯዊ ሁኔታ የተከሰተው ድርቅና አሁንም ድረስ በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት በትምህርቱ ዘርፉ የክልሉን ሀገራዊ ተወዳዳሪነት እየተገዳደረው እንደሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ተናግረዋል:: ግጭቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት የታቀደውን የትምህርት ይዘት ለማጠናቀቅ ፈተና ከመሆኑም ባለፈ እንደ ክልል ተቀብሎ ለማስተማር የታሰበው የተማሪ ቁጥር ለማሳካት ፈተና መሆኑን አንስተዋል::
በ2016 የትምህርት ዘመን ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ቢታቀድም እስካሁን ማሳካት የተቻለው ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብቻ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል:: ይህም ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ለዕቅዱ አለመሳካት ማሳያ ነው ብለዋል:: የጸጥታ ችግሩ ሦስት ሺህ የአንደኛ ደረጃ እና 225 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስካሁን ወደ መማር ማስተማር እንዳይሸጋገሩም አድርጓል::
እንደ መፍትሄ
መ/ር ሸጋው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሰረት አድርገው እንደተናገሩት በግጭት ጊዜ ትምህርትን ማስጀመር እንደ ሥነ ልቦና ድጋፍ ይወሰዳል:: በኢትዮጵያ ግን ይህንን ማድረግ አልተቻለም:: ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ዋና ፈተናው ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮች ውጤት ነው ይላሉ:: በመሆኑም ችግሮችን ለይቶ አንድ በአንድ መፍትሄ መስጠት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል::
ሕዝቡ ለትምህርት እና ለተማረ አካል የሚሰጠው ቦታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መጥቷል ያሉት ባለሙያው፣ ለዚህም ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ በማካሄድ ትምህርት የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳድር መሰረት መሆኑን ማስረጽ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በፍትሐዊነት ማልማትም ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም ችግር ፈቺ ትውልድ ለማፍራት ዋና መፍትሄ መሆኑን አመላክተዋል::
ተደራሽነትንም ሆነ ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሀብት የሚያስፈልግ ቢሆንም ጥራትን ለማምጣት ሽፋንን ለማሳደግ ከሚመደበው በላይ ገንዘብ ማፍሰስ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: ለዚህም በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚደረገውን የኢንቨስትመንት መጠን መጨመር እንደሚገባ ያምናሉ:: ይህም የተሻሉ መማሪያ ክፍሎች ያሏቸውን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት፣ መምህራንን በስልጠና ለማብቃት፣ የትምህርት ግብዓትን በሚፈለገው መጠን ጊዜ ሳይሰጡ ለማሟላት ያግዛል::
ትምህርትን በቴክኖሎጂ መደገፍ ለጥራትና ተደራሽነት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ባለሙያው ጠቁመዋል:: በተለይም የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት ባለሙያው ሲያስረዱ፤ “ልክ እንደ አሁኑ ወቅት በግጭት ምክንያት ትምህርት ቤት ሂዶ ለመማር በማይቻልበት ወቅት ትምህርቱን በቴክኖሎጂ ታግዞ ማስቀጠል ይቻላል:: ይህም ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና መምህራንን ከሥነ ልቦና ጉዳት ከመታደጉም ባሻገር ዓለም የምትፈልገው ትውልድ ለመፍጠር የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው::”
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሞኑ በጎንደር፣ በደብረ ብርሐን እና በሌሎችም ከተሞች ከሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል:: በመድረኮቹ የተገኙት የቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር ከመሥራት ጎን ለጎን በትምህርት ላይ የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል::
ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ሀገር ያጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች እና ሌሎች ምክንያቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል:: የክልሉን የማሳለፍ ምጣኔ ለማሳደግም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ ንቅናቄ ሲደረግ ቆይቷል::
ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ እስካሁን 41 በመቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይመጡ ማድረጉን የቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀዋል:: ይህም አሁንም ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚገቡ ተማሪዎች ላይ ጫና እንደሚፈጥር ታምኖበታል:: የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውሳኔ የትምህርት ሚኒስቴር ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ እስካሁን ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎች ለፈተና እንደማይቀመጡ ገልጸዋል:: በቀሩት ጊዜያት ትምህርት አስጀምሮ ይዘቶችን በአግባቡ ሸፍኖ ለፈተና ብቁ ማድረግ አለመቻሉን ምክንያት አድርገው አቅርበዋል:: በትምህርት ላይ ያሉትን ግን ለፈተና ዝግጁ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *