ግጭቱ ትምህርቱን ፈትኖታል

በአማራ ክልል ግጭት ከተከሰተ ስምንት ወራትን ተሻግሯል። ይህም ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተዳደር አድርጎታል። በሰሜኑ ጦርነት ከ522 ቢሊዮን ብር ቁሳዊ ጉዳት ያስተናገደው ክልሉ ታዲያ አሁናዊ ግጭቱ የክልሉን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል።
በግጭቱ በርካታ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በመስከረም ወር መጀመሪያ እንዳስታወቀው በወቅቱ መመዝገብ ከሚገባቸው ከግማሽ የሚበልጡት አልተመዘገቡም ነበር። ግጭቱ ተባብሶ በመቀጠሉም ወደ ትምህርት ገበታ የመሄድ ዕድል የሚኖራቸው እጅግ ውስኑ ለመሆናቸው አመላካች ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ፈተናዎች እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ። በሌላ በኩል በአማራ ክልል በአማካኝ አንድ መጽሐፍ ለ70 ተማሪዎች የደረሰበት አካባቢዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን እንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሰሞኑን እንዳስታወቀው የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማስፈተን ተማሪዎችን በበይነ መረብ የመመዝገብ ሥራ እየተሠራ ነው። የቢሮው ምክትል ኃላፊ እየሩስ መንግሥቱ የ6ኛ ክፍል ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል አቀፍ ደረጃ እንደሚሰጥ ተናግረዋል:: የ8ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚሰጥ ነው የገለጹት::
በሰባት ሺህ 543 ትምህርት ቤቶች የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዋ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባ እያካሄዱ ያሉት አምስት ሺህ 421 ትምህርት ቤቶች ናቸው ብለዋል::
የተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ በበይነ መረብ እየተካሄደ እንደነበር ቢነገርም በክልሉ ኢንተርኔት ከተቋረጠ ከስምንት ወራት በላይ ሆኗል። አሁንም እንደተቋረጠ ነው።
ምክትል ኃላፊዋ እንዳሉት ፈተናው በሁለት ዙር ይሰጣል። ቀድመው የተመዘገቡት ተማሪዎች ደግሞ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም እንደሚፈተኑ ገልጸዋል:: ዘግይተው ከተመዘገቡት መካከል ላይ ያቆራረጡ እና መማር ያለባቸውን ትምህርት በአግባቡ ያልተማሩ ተማሪዎች የሁለተኛ መፈተኛ ጊዜ ይኖራቸዋል ብለዋል:: ተማሪዎች በየትኛው የመፈተኛ ጊዜ መፈተን እንደሚፈልጉ ለመወሰን ከተማሪዎች እና ከወላጆች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በተለይም የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተና የሚወስዱት ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ መደናገጥ እንዳይኖር በሥነ ልቦና የማጠንከር ሥራዎች እየተሠራ ነው ብለዋል::
በ2015 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም 14 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን መጻሕፍት ማሳተማቸውንም ምክትል ኃላፊዋ አስታውቀዋል:: ከታተሙት መጻሕፍት መካከል ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን መጻሕፍት ማሰራጨታቸውንም ገልጸዋል:: ለ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የመጽሐፍት ስርጭት የተሻለ መኾኑን እና በ2ኛ ደረጃ ላይ ግን እጥረቶች መኖራቸውን ነው ያነሱት:: በቀጣይም የመጻሕፍት ሕትመቶች እንደሚኖሩም አመላክተዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል በአማካኝ አንድ መጽሐፍ ለ70 ተማሪዎች የደረሰበት አካባቢዎች መኖራቸዉን ማረጋገጡን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አረጋግጫለው ብሏል:: በተቋሙ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ በክልሉ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ተቋሙ ጥናት አካሂዷል፤ በጥናቱም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች የመጽሐፍ ጥምርታ በአማካኝ አንደ መጽሐፍ ለ60 ተማሪ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ አንድ መጽሐፍ ለ70 ተማሪ መሆኑን ነው የሕዝብ እንባ ጠባቂ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ጋሻነው ደሴ ለበኩር ጋዜጣ የተናገሩት።
ለተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት በሶፍት ኮፒ ቢሰጥም ተማሪዎች ማንበቢያ ማለትም እንደ ስልክ፣ ታብሌት እና ላፕቶፕ ስለሌላቸው እየተቸገሩ ነው፤ ይህም በትምህርት ጥራት ላይ ችግር እያስከተለ ነው ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በባሕር ዳር ከተማ በተደረገ ክትትል 57 መምህራን ያልተማሩትን እንደሚያስተምሩ ማረጋገጡን አቶ ጋሻነው ተናግረዋል፡፡
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *