“ትምህርት ለተሻለ ሕይዎት ማዘጋጃ ብቻ ሳይኾን ራሱ ሕይዎት ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር: መሥከረም 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) “ትምህርት ለተሻለ ሕይዎት ማዘጋጃ ብቻ ሳይኾን ራሱ ሕይዎት ነው” ብለዋል። “የመጀመሪያውን ምዕራፍ፣ በጥረታችሁ እና በድካማችሁ በውጤታማነት በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ሌሎች ከእናንተ ውጤታማነት ትምህርት እንዲወስዱ እንሸልማችኋለን” ነው ያሏቸው።
የበርካታ ምሁራን መፍለቂያ የኾነው የአማራ ክልል ዛሬም ምርጥ ተማሪዎችን እያፈራ መኾኑንም ተናግረዋል። የምርጦችን ምርጥ መሸለም ተከታዮች ትኩረት እንዲሰጡ እና ትምህርት እንዲወስዱ ለማሳሰብ ነው ብለዋል።
“ሕይዎት ረጅም መንገድ ነው” ያሉት ኀላፊዋ ረጅሙን መንገድ አንዳንዶቹ በጨለማ፣ ብልሆቹ ደግሞ በብርሃን ይጓዙታል ነው ያሉት። የሰው ልጅ ራሱን የሚቀይርበት እና የሕይዎት ጉዞውን ተስፋ የሚያንጸባርቅበት ትልቁ መሳሪያ ትምህርት መኾኑንም ገልጸዋል።
ትምህርት የሰው ልጅ አዕምሮን ያሠለጥናል፣ ሃብቶችን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጋል፣ እሳቤውም ጭምር እንዲያድግ ያደርጋል ነው ያሉት።
ጸጋዎቻቸውን በትክክል የተረዱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ሁሉ በብልሃት ያልፋሉ ብለዋል። የሰው ልጅ ሕይዎት ቀለል እንዲል ያደረጉ ሥራዎች መነሻቸው እና መድረሻቸው ትምህርት መኾኑን ነው የተናገሩት።
በሳይንስ እና ቴክኖሎጅ የበለጸጉ ሀገራት የዕድገታቸው ምስጢር የሰው ሃብታቸውን በብቃት ማልማት በመቻላቸው ነው ብለዋል።
የሰው ሃብት የሚለማው በትምህርት መኾኑን ነው የተናገሩት። የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስነው የተማረው ትውልድ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ወደ ትምህርት እንዲሄዱ እንደሚፈለግ የተናገሩት ኀላፊዋ በክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ በርካታ ሕጻናት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትምህርት ገበታ አልመጡም ብለዋል። ለዚህ የዳረጉት ደግሞ ግጭት እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ናቸው ነው ያሉት።
ግጭት የሚፈታው እና ድህነት የሚረታው በትምህርት መኾኑንም ገልጸዋል። ለትምህርት ያለው አረዳድ፣ ትኩረት እና ድጋፍ ከፍ ማለት አለበትም ብለዋል።
በሥነ ምግባር የተገነቡ፣ በአመለካከት እና በዕውቀት የዳበሩ፣ ቴክኖሎጅን የሚጠቀሙ፣ ሥራ ፈጣሪ እና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ለማፍራት ሁሉም ብርቱ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት።
ለወደፊቱ የሚገኙትን ጸጋዎች እና ፈተናዎች እንደየአመጣጣቸው ተቀብለው በድል ለመወጣት እና ተግዳሮቶችን ለመሻገር፣ ሀገርንም ለማሻገር ከፍተኛ ጥንካሬ፣ የተወዳዳሪነት ሥነ ልቦና ያስፈልጋል ብለዋቸዋል።
አልጋ በአልጋ የሚኾን ጉዞ እንደሌለ ያሳሰቡት ኀላፊዋ ከዚህ በላይ ጠንክረው እና ተግተው ሀገራቸውን እንዲያሻግሩ አደራ ብለዋል። ጅምራቸው መልካም ስለኾነ አደራውን እንደሚወጡም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የገጠመውን የትምህርት ስብራት ለመፍታት አዲስ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል። በተደረገው ለውጥም በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።
ሀገር ወዳድ፣ ባሕል እና እሴቱን የሚጠብቅ፣ ኩረጃን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት ጥረቶች ተደርገዋል ነው ያሉት።
በትምህርት ላይ የሚደረጉ ለውጦች በአንድ ጊዜ የማይታዩ ባለመኾናቸው ጊዜ ይፈልጋሉ ያሉት ኀላፊዋ ያም ኾኖ እየተደረጉ ያሉ ለውጦች ትምህርትን ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት አይነተኛ መፍትሔዎች ናቸው ብለዋል።
መንግሥት ለትምህርት ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል። የክልሉ ትምህርት በዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢፈተንም በተረባረበ ተሳትፎ አስደናቂ ውጤቶች እየተገኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ባለፉት ዓመታት በተሰጡ ብሔራዊ ፈተናዎች የአማራ ክልል ተማሪዎችን በማሳለፍ ግንባር ቀደም መኾኑንም ተናግረዋል። እየተገኘ ያለው ውጤት በርትተን እንድንሠራ ትልቅ በር የሚከፍት ነውም ብለዋል።
ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሁሉ ምንም ያላሰለፉ ትምህርት ቤቶችም አሉ ያሉት ኀላፊዋ የሠሩትን መሸለም፣ ዝቅ ያሉትን ደግሞ ማስተካከል የ2017 ዓ.ም ልዩ ትኩረት ነው ብለዋል።
ተማሪዎችን ለማገዝ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። ትውልድን ለማስቀጠል ለሠሩ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። የተገኘው ውጤት እና ጥረት በሰላም ጊዜ ኾኖ ቢኾን ደግሞ ከዚህ የላቀ ይኾን ነበር ነው ያሉት።
መንግሥት የትምህርት ግብዓት ለማሟላት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ባለድርሻ አካላትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።
ተማሪዎች ኢትዮጵያን ለማሳደግ በቁ እና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪ እንዲኾኑም አሳስበዋል። የሚገጥማቸውን ችግር በጥበብ እንዲፈቱም አስገንዝበዋል።
“የፖለቲካ ልዩነት ያለ፣ የነበረ እና የሚኖር ነው” ያሉት ኀላፊዋ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት የሥልጡን ሕዝብ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል። የነገ ልጆች ትውልድ ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል። ተማሪዎች የየትኛውም የፖለቲካ መጠቀሚያ ሳይኾኑ የራሳቸውን የነገ ዕድላቸውን ወስነው ተወዳዳሪ መኾን ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ትምህርት በአግባቡ እንዲሰጥ፣ ጥራቱ እና ተሳትፎውም እንዲቀጥል ሁሉም ማኀበረሰብ እንዲሠራ አሳስበዋል።
ዛሬ የተሸለሙ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ስኬታማ እንዲኾኑ አሳስበዋል። ሀገራቸውን እንደሚያኮሩም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።