“ችግርን እንደበጎ መነሻ መውሰድ ይገባል” ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ጌታቸው እያዩ
ባሕር ዳር: መሥከረም 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል። በችግር ውስጥ አልፈው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችም በተደረገው ሽልማት ደስተኞች መኾናቸውን ተናግረዋል።
ተማሪ ሰለሞን ጸጋ በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከደብረታቦር ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው የመጣው። በ2016 የትምህርት ዘመን የተሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በከፍተኛ ውጤት ያለፈ ነው። ከዚህ የተሻለ ውጤት ጠብቆ እንደነበር ተማሪው ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኾኖ ከተመዘገበው ውጤት በላይ ጠብቆ እንደነበር ነው ያስታወሰው።
“ውጤቱን እንዳየሁ ደስተኛ አልነበርኩም፣ ምክንያቱም ከዚህ በላይ ጠብቄ ነበር” ነው ያለው።
በተሰጣቸው የማበረታቻ ሽልማት ግን ደስተኛ መኾኑን ነው የተናገረው።
ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እና ሲፈተኑም በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾነው እንደነበር ገልጿል።
“ፈተና ላንፈተን እንችላለን ብለን ሰግተን ነበር፣ ነገር ግን በዚያ ችግር ውስጥ ተፈትነን እንደጠበኩትም ባይኾን ከፍተኛ ውጤት በማምጣቴ ደስተኛ ነኝ” ነው ያለው።
ለውጤት እንዲበቃ ከፈጣሪ ቀጥሎ ቤተሰቦቹ፣ መምህራን እና የትምህርት ቤት ሠራተኞች አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መኾኑን ገልጿል።
በጸጥታ ችግሩ ትምህርት ስለሚቆራረጥ ተማሪዎች ተስፋ ያጡ እንደነበር ገልጿል። ነገር ግን ይላል ሰለሞን ጥሩ ነገር ባይመጣም መልካሙን ተስፋ ማድረግ መልካም ነው ብሏል።
ሰዓቱን በሚገባ እንደሚጠቀምም ተናግሯል። ተስፋ እያደረጉ ሰዓትን መጠቀም ውጤታማ ያደርጋል ነው ያለው።
ሰዓቱን ባይጠቀም ኖሮ ውጤቱ ዝቅተኛ ይኾን እንደነበርም ተናግሯል። ተማሪዎች ምንም የከፋ ችግር ቢመጣም ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም ብሏል።
የተማሪ ሰለሞን ቤተሰብ ትዕግሥት መንግሥቴ በችግር ውስጥ አልፎ ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ ደስተኞች ነን ብለዋል። ከውጤቱ በተስተጀርባ ጠንካራ ወላጆች አሉት ነው ያሉት። ጊዜውን በአግባቡ የሚጠቀም፣ ትሁት እና ታታሪ ነው ብለዋል። ከእርሱ ብዙ ነገር እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ከፍተኛውን ውጤት ያመጣው ከደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ጌታቸው እያዩ ለተደረገላቸው የማበረታቻ ሽልማት ደስተኛ መኾኑን ተናግሯል። እንዲህ ሲታሰብልን እኛም ደግሞ ከፍ ያለ ነገር እናስባለን ነው ያለው።
ውጤቱን እንዲያመጣ የመምህራን፣ የወላጆች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተናግሯል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለትምህርት አስቸጋሪ ነው የሚለው ተማሪ ጌታቸው ችግርን ለመልካም ነገር መጠቀም ከተቻለ ግን ስኬታማ ያደርጋል ነው ያለው።
ለአብነት ይላል ተማሪ ጌታቸው ከደሃ ቤተሰብ የወጣ ልጅ የቤተሰቦቹን ደህነት ለመቀየር እንደመነሻ ከተጠቀመው የሚያቆመው የለም፣ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር በመቋቋም እንደመነሻ ከተጠቀምነው የበለጠ ያበረታናል ነው ያለው።
ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር እንደበጎ መነሻ መውሰድ አለባቸው ብሏል።
ከባሕርዳር ኤስኦኤስ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ሙሉዬ ዓባይ “ለተደረገልን ሁሉ እናመሠግናለን” ነው ያለችው።
እናቷ፣ መምህራን እና ትምህርት ቤቱ ውጤቷ እንዲያምር አስተዋጽኦአቸው ሰፊ እንደነበር ተናግራለች።
ቀጣይ የሚፈተኑ ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ መዘጋጀት እንደሚገባቸው መክራለች።
የብሔራዊ ፈተና ሊደርስ ሲል ብቻ ወደ ጥናት መዞር ውጤታማ እንደማያደርግ ነው የተናገረችው።
የተማሪ ሙሉዬ ወላጅ እናት አልማዝ መንግሥቴ በልጃቸው ውጤት ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል ።
ለተመዘገበው ውጤት የእርሳቸው አስተዋጽኦም እንዳለበት ነው የተናገሩት።
ልጃቸው የምትፈልገውን ነገር እንደሚያሟሉላትም ገልጸዋል።
ሌሎች ወላጆችም ልጆቻቸውን መከታተል መጠየቅ፣ በግልጽ መቅረብ አለባቸው ብለዋል።
ግልጸኝነት ሲኖር ልጆች በነጻነት እንደሚጠይቁ እና ከአልባሌ ነገርም እንደሚቆጠቡ አብራርተዋል።
ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ መስጠት እና መጠየቅ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።