ከ12 ሽህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እያገኙ ነው። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር
የትምህርት ቤት ምገባ መኖሩ በጠዋት ተነስቸ አራት ልጆቸን ቁርስ ምን ላብላቸው ከሚል ሰቀቀን ታድጎኛል። አራት ልጆቿ የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ የሆኑላት እናት።
ትምህርት ቢሮ /ታህሳስ 19/2017 ዓ.ም/ በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከ12 ሽህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግስቱ አበበ ከ75 ሚልዬን ብር በላይ በሆነ ወጭ በ16 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ከ12 ሽህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ምገባውን ለማከናወን ከተማ አስተዳደሩ 50 ሚሊዬን ብር የመደበ ሲሆን ከማህበረሰቡና ከአጋር ድርጅቶች የ25 ሚሊየን ብር አስተዋጽኦ ይጠበቃል። ህብረተሰቡና አጋር ድርጅቶች ለትምህርት ቤት ምገባ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን በአንድ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ቀን ብቻ አስር ነጥብ አምስት ሚሊዬን ብር ቃል መገባቱን አቶ መንግስቱ ተናግረዋል።
ወደፊት የትምህርት ቤት ምገባን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር የምገባ ቦርድ ተቋቋሞ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል።
ማህበረሰቡ ለትምህርት ቤት ምገባ ገንዘብ ከማዋጣት ባለፈ በየትምህርት ቤቱ የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾችን በርብርብ መገንባቱን በመስክ ተዘዋውረን ተመልክተናል።
የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ቤት ምገባ ዘላቂነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት መምሪያ ኃላፊው ለዚህም ከአንድ የከተማ አስተዳደር ህንጻ የሚገኝ የኪራይ ገቢን ለትምህርት ቤት ምገባ እንዲውል መፍቀዱን አመላክተዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ መኖሩ በጠዋት ተነስቸ አራት ልጆቸን ቁርስ ምን ላብላቸው ከሚል ሰቀቀን እንደታደጋት ወይዘሮ ሰዓዳ ከበደ ነግራናለች።
ሰዓዳ የኮምቦቻ ከተማ ነዋሪ ስትሆን በአሁኑ ወቅት ባለቤቷ ከጎኗ ባለመኖሩ ከሴፍቲኔት በምታገኛት አነስተኛ ገቢ በኮምቦልቻ ቁጥር ሁለት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አራት ልጆቿን ታስተምራለች።
ልጆቿ በትምህርት ቤቱ በሚያገኙት የዳቦና ወተት ምገባ አገልግሎት ደስተኛ በመሆናቸው ትምህታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን ገልጻ እሷም በየቀኑ ለልጆቿ ቁርስ ዳቦ ለመመገብ ብቻ ታወጣ የነበረውን ከ40 ብር በላይ ወጭ የቀነሰላት መሆኑን ገልጻለች።
የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት መኖሩ በትምህርት ቤታቸው ከዚህ በፊት ያጋጥም የነበረውን የተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ ማሳለስና የማርፈድ ምጣኔ መቅረፉንና ተማሪዎች በአካልና በአእምሮ ንቁ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉን የኮምቦልቻ ቁጥር ሁለት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አበበ ብርሃኑ ገልጸዋል ።
ሳይንሳዊ ጥናቶችና በየጊዜው የሚደረጉ ውጤት ትንተናዎች እንደሚያሳዩት የትምህርት ቤት ምገባ ለተማሪዎች ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎችን በትምህርታቸው ውጤታማ ከማድረጉ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልና የገበያ ትስስር ፈጥሯል። በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የሚከናወነው የትምህርት ቤት ምገባ ለስምንት ዳቦ አምራች ኢንተርፕራይዞችና ለሶስት ፖስቸራይዝድ ወተት ለሚያቀርቡ ድርጅቶች የገበያ ትስስር ፈጥሯል።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z