ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎች እንዲመለሱ ባለድርሻ አካላት የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ተባለ።
ባህር ዳር፣ ጥር፣ 2/2017ዓ.ም ( ትምህርት ቢሮ ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዪኒኬሽን ቢሮ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመተባበር በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶችንና ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየተደረገ ያለውን እርብርብ አስመልከቶ የፓናል ውይይት መድረክ አካሂድዋል ::
ትምህርት ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ እና ቴክኖሎጅካዊ እድገት መሰረት የሆነ ዘርፍ ቢሆንም በክልሉ ያሉ 3 ሽህ በላይ የትምህርት ተቋማት በርካታ ችግሮች ውስጥ መሆናቸውን የትምህርት ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ባቀረቡት የውይይት ሰነድ ገልፀዋል።
ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሲደረግ የትምህርት ተሳትፎው ግቡን አሳካ ይባላል፤ የአማራ ክልል የትምህርት ተሳትፎ ከተወሰኑ አመታት ወዲህ እየቀነሰ ነው። ከ2012ዓ/ም ጀምሮ በኮቪድ _19 ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነትና አሁን ላይ ክልሉ በገጠመው የሰላም ችግር የትምህርት ተሳትፎ እየቀነሰ መምጣቱን በቀረበው ሰነድ አመላክተዋል።
ትምህርት ቤቶች ከየትኛውም የፖለቲካ አጀንዳ ነፃ ሁነው ለትውልድ እውቀት የሚገነቡ ቢሆንም ክልሉ በገጠመው ችግር ከትምህርታቸው የተገለሉ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ተማሪዎቹ ለስነ ልቦናዊ እና ለማህበራዊ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ትምህርት ቢሮው አቅዶ እየሰራ ቢሆንም በተፈጠረው የሰላም እጦት በክልሉ የተማረ የሰው ኃይል ለመፍጠር የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት አስቸጋሪ ሆኗል ያሉት አቶ ጌታቸው በተለይም መምህራን እየከፈሉት ያለውን ዋጋ ትውልድ የማይረሳው በመሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና የክልሉ ህዝብ በሙሉ ልጆቻቸው በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ መምከር እንዳለባቸው አሳስበዋል ::
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ዘበነ የትውልድን ትስስርና ውጤታማ ቀጣይነት ማረጋገጫ አቅም በሆነው የትምህርት ሥራ ላይ የገጠመው ችግር በሁሉም አካላት ርብርብ መስተካከል እንዳለበት ገልፀዋል።
ሀገር ተረካቢ ሕፃናት ወደ ትምህርት ተቋማት ሄደው በመማር ነገን የተሻለ ትውልድ ለማስቀጠል ተማሪዎች መሰረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው የተረጋጋ ትምህርት እንዲማሩ የሚደረገው ጥረት ትልቅ ዋጋ እንዳለውም አቶ ሙሉነህ አክለው ተናግረዋል።
ትናንት በተፈጠረ የትምህርት ስብራት ምክንያት ትውልድን ለማስቀጠል ብዙ ፈተናዎችን አይተናል ሲሉ የገለፁት የክልሉ የመንግስት ኮሙኒከሽን ቢሮ ም/ኃላፊ ወ /ሮ ትብለጥ መንገሻ በበኩላቸው አሁን በክልሉ የተፈጠረው ችግር ሕፃናት የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲቀንስ ከማድረጉም ባሻገር ለስደት፣ ለፆታዊ ጥቃትና ለሱሰኝነት እየተዳረጉ ሲሆን ብዙ መምህራንም ሞተዋል፤ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል ሲሉ ገልፀዋል ::
በትምህርት አሰጣጥ ላይ የገጠመው ችግር እንዲስተካከል ማህበረሰቡን ማስገንዘብን ጨምሮ ሚዲያዎችም አገር በመገንባት ሂደት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲሉም ወ/ሮ ትብለጥ አሳስበዋል ::
በተሳታፊዎች በኩልም ትምህርት ትውልድን ማስቀጠል እንዲቻል ሁሉም ማህበረሰብ የችግሩን ደረጃ እንዲረዳው ማስገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል።ለዚህም የየድርሻቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *