የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው። በግምገማ መድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አንስተዋል።
* በአለም ታሪክ ሆነ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሁሉ መፍተሔ የሚያፈልቀውና መውጫው መንገዶችን የሚቀይሰው ትምህርት ነው።
* ትምህርት ሰባዊ ሀብትን በማፍራት በኩል ተኪ የለሽ ሚና አለው። ሀገር በቀል እውቀትን የሚረዳና የበለጠ የሚያሳድግ ቴክኖሎጅን የሚያፈልቅና የሚጠቀም በስነ ምግባር የተመሰገነ ፣ በአመለካከትና በእውቀት የዳበረ፣ ስራ ፈጣሪና ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሆነ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ለማፍራት አርቆ ማሰብ በትልቁ ማቀድና አብልጦ መተግበርን ያስፈልጋል፡፡
* ባለፈው ስርዓት የተማረው ትውልድ ሀገር በቀል እውቀት የራቀው፣ ደራሽ የሆኑ ሀሳቦች የሚያናውጡት በመሆኑ ሀገር ለችግር ተዳርጋለች።
* የአማራ ክልል ትምህርት በሰሜን ጦርነት ወቅት የጦርነት አውድማ በመሆኑ ምክንያት በትምህርት ተቋማት፣ በመምህራንና ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
* አሁንም በክልላችን በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ዋነኛው ተጎጅ ትምህርት ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች ከትሞህርት ገበታ ውጭ ናቸው። በ2016 የትምህርት ዘመን መማር ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 58% የሚሆኑት ብቻ ናቸው መማር የቻሉት። በጽንፈኞች በታወጀ ጦርነት፣ በመምህራንና ተማሪዎች ላይ በሚደርስ እንግልትና ጫና በትምህርት ጠል ፕሮፖጋንዳ ምክንያት በዚህ ዓመት ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው። ከተመዘገቡት መካከል ከአራት መቶ ሽህ በላይ የሚሆኑት ትምህርታቸውን መማር አልቻሉም። በተሳትፎም በጥራትም ቀዳሚ የነበረ ክልል ዛሬ ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጓል።
* ከጥቂት አመታት በኋላ በየዩኒቨርሲቲው ልጇን የምታስመርቅ የአማራ እናት አትኖርም።
* ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎቻችን ቁጥር በዓለም ላይ ከ106 ሀገራት፣ በአፍሪካ ከ14 ሀገራት፣ በሀገራችን ከ6 ክልሎች የህዝብ ቁጥር ይልቃል።
* ለትምህርት ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት ያለውን የአማራ ክልል ህዝብ እንዳይማር መከልከል ከበደል በላይ በደል ነው
* አለም በላቀበትና በሰለጠነበት በዚህ ዘመን አለመማር ራስን እንደማጥፋት ይቆጠራል።
* በተለይም ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለስደት፣ ለሱስ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ ለስነልቦና ጫና ተዳርገዋል። መምህራን ሞተዋል፣ ታግተዋል ፣ለስቃይና ያልተገባ እንግልት ተዳርገዋል።
* ዛሬ ካላስተማርን ነገ ስንታመም የሚያክመን ሀኪም፣ ልጆቻችን የሚያስተምር መምህር፣ ቤታችንን የሚገነባ መሀንዲስ፣ በየዘርፉ የሚያስፈልገን የሰለጠነ የሰው ሀይል አይኖረንም።
ትውልድን በማደንቆር የሚጠቀም ትውልድ አይኖርም።
መምህራን ሲገደሉ ሲታገቱ፣ ሲሰቃዩ መምህራን ማህበር፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና መላው ማህበረሰብ ሊያወግዝ ይገባል።
ትምሀርት ለየትኛም የፖለቲካ አላማ ውግንና ሊውል አይገባም።
አሁንም ተስፋ አለን
ትምህርት ለትውልድ የንቅናቄ መድረኮች በዞን በወረዳና በአንዳንድ አካባቢዎች በቀበሌ ደረጃ ተካሂደዋል። ህብረተሰቡም ልጆቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው ቁጭቱን ተናግሯል።
ተማሪ ምዝገባ በሁለት ዙር ተካሂዷል። አሁንም የተማሪም
ምዝገባን አጠናክረን እንቀጥላለን። የተመዘገቡትን ሁሉ ማስተማር፣ የ6ኛ ፣የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ማብቃት፣ ሀብት በማፈላለግ የትምህርት ቤቶቻችንን ደረጃ ማሻሻል በትኩረት መስራት ይገባናል።
ህዝቡ በችግር ውስጥ ሆኖ ትምህርት ቤት እየገነባ ነው።
ለልጆቻችን እውቀትና ብርሀን ለመስጠት ሲደክሙ በጽንፈኞች ጉዳት የደረሰባቸውን መምህራን ከጎናቸው ልንሆን ይገባል።
የትምህርት ቤት ምገባን የበለጠ ማስፋፋት ላይ እንሰራለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *